የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ዘመንን በተመለከተ ማወቅ ያለብን ነጥቦች
በቅርቡ በወጣው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016፣ የተከራይና የአከራይን መብትና ግዴታ የሚወሰኑ አዳዲስ ድንጋጌዎች ተካተዋል። ከእነዚህም መካከል የኪራይ ውል ዘመንን በተመለከተ የሚከተሉት ነጥቦች ተጠቃሽ ናቸው። ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ከሁለት ዓመት ላነሰ ጊዜ ሊደረግ አይችልም። አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በጽሑፍ የተደረጉ ውሎች ግን በውሉ ላይ በነበራቸው የውል ዘመን ይቀጥላሉ። አንድ የመኖሪያ ቤት በሽያጭ፣ በውርስ፣ በዕዳ ወይም በሌላ ማናቸውም ሕጋዊ ምክንያት ለሌላ ሰው ከተላለፈ፣ አዲሱ ባለቤት ተከራዩን ለማስወጣት የ6 ወር የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ አለበት። ቤቱ ለሌላ ሰው የተላለፈው በስጦታ ከሆነ ግን፣ ተከራዩ የነበረውን የኪራይ ውል ዘመን እስኪያጠናቅቅ ድረስ በቤቱ የመቆየት መብት አለው። ስጦታ የተቀበለው ሰውም የአከራዩን መብትና ግዴታ ወርሶ የአከራዩን መብትና ግዴታ ይሸከማል።
በባለቤትነት ለውጥ ምክንያት የኪራይ ውል ተቋርጦ ቤቱ ለሌላ ተከራይ የሚሰጥ ከሆነ፣ አዲሱ የኪራይ ዋጋ ቀድሞ በነበረው ውል ላይ ከተጠቀሰው ዋጋ መብለጥ የለበትም (በአዋጁ መሠረት ከሚደረግ ጭማሪ ውጭ)። የኪራይ ውል ዘመን ሳይጠናቀቅ ተከራይን ማስወጣት የተከለከለ ነው። በአዋጁ ከተፈቀደው ውጭ፣ የውል ዘመን ሳይጠናቀቅ የኪራይ ዋጋ መጨመር በሕግ የተከለከለ ነው።

(0) comments to this article
No Reviews