Loading......
template-img

እውቅና እና ሀገርነት በዓለም አቀፍ ሕግ

በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አንድ አካል ሀገር ለመባል ማሟላት ስላለባቸው መስፈርቶች በ1933ቱ የሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽን (Montevideo Convention) አንቀጽ 1 ላይ ተደንግጎ ይገኛል። በዚህ ኮንቬንሽን ላይ የሀገርነት አራት መስፈርቶች (The Four Criteria for Statehood) ተቀምጠው ይገኛሉ። የመጀመሪያው መስፈርት ቋሚ ሕዝብ (A Permanent Population) መኖር ነው። በሀገሪቱ ክልል በቋሚነት የሰፈረ እና የሚኖር የሰዎች ስብስብ ሊኖር ያስፈልጋል። የሕዝቡ ብዛት መጠንን በተመለከተ የተቀመጠ ገደብ የለም። ሕዝቡ የዜግነት መብት ያለው ወይም የሌለው ተቀላቅሎ ሊሆን ይችላል። ሕዝቡ አርብቶ አደር ወይም ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ሊኖር ይችላል። ይህ የሕዝቡ የአኗኗር ዘይቤ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ዋናው ነገር ሕዝቡ በተወሰነው ክልል ውስጥ ለዘለቄታው የሚኖር መሆኑ ነው። ሁለተኛው መስፈርት የተወሰነ ክልል (A Defined Territory) መኖር ነው። ሀገሪቱ የምትቆጣጠረው እና የሉዓላዊነት ሥልጣኗን የምታሳርፍበት መሬት፣ ውሃ እና የአየር ክልል መኖር ማለት ነው። ልብ ሊባል የሚገባው የክልሉ ወሰን የግድ ሙሉ በሙሉ በሌሎች ሀገራት የታወቀ ወይም ከክርክር ነጻ መሆን የለበትም። በዓለም ላይ ብዙ የወሰን ግጭቶች ያሉባቸው ሀገራት አሉ፣ ግን ይህ ሀገር መሆናቸውን አያሳጣም። አስፈላጊው ነገር ውጤታማ ቁጥጥር የሚደረግበት የተወሰነ ክልል መኖር ነው። ሦስተኛው መስፈርት ደግሞ መንግሥት (A Government) ሊኖር ይገባል። ይህ መንግሥት በክልሉ ላይ ያለውን ሥልጣን በብቃት የሚጠቀም እና ሕግና ሥርዓት ማስከበር የሚችል የፖለቲካዊ ቁጥጥር አካል መኖር ማለት ነው። ልብ ሊባል የሚገባው መንግሥቱ በዲሞክራሲያዊ መንገድ መመረጡ ወይም በሌላ መንገድ ሥልጣን ላይ መውጣቱ በዓለም አቀፍ ሕግ ዘንድ በመስፈርትነት የተቀመጠ አይደለም። ምንም እንኳን አንዳንድ አካላት/ ሀገራት እውቅና ለመስጠት እንደ መስፈርት ሊያዩት ቢችሉም። አስፈላጊው ነገር መንግሥቱ በግዛቱ ውስጥ ውጤታማ ቁጥጥር ያለው መሆኑ ነው። ማለትም በክልሉ ውስጥ ያለውን ሕዝብ መቆጣጠር እና መወከል መቻል አለበት። እዚህ ጋር በጥያቄነት የሚነሳው አንድ መንግሥት የመቆጣጠር አቅሙን ሙሉ በሙሉ ካጣ (Failed State) የአንድ ሀገር ሀገርነት (Statehood) ቀሪ ሊሆን ይችላል ወይ? የሚለው ነው።

በሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽን ላይ የተቀመጠው አራተኛው መስፈርት ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነት የመፍጠር ችሎታ (Capacity to Enter into Relations with Other States) ነው። ሀገሪቱ ሉዓላዊ፣ ነፃ እና ከማንኛውም ውጫዊ ቁጥጥር ነፃ ልትሆን ይገባል። ይህ ማለት የራሷን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመወሰን እና ስምምነቶችን የመዋዋል ሙሉ መብት ሊኖራት ይገባል። ልብ ሊባል የሚገባው ይህ መስፈርት የሚያተኩረው በዋናነት ሉዓላዊነት (Sovereignty) ላይ ነው። አንድ አካል የሌላ ሀገር አካል ወይም ጥገኛ ከሆነ ይህን መስፈርት አያሟላም። አንድ ሀገር የውጭ ግንኙነቶቿን በሙሉ ለሌላ ሀገር በአደራ መስጠት ትችላለች፣ ነገር ግን ይህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። እንግዲህ በሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽን መሰረት አንድ አካል ሀገር ለመሆን የተቀመጡት መስፈርቶች ከላይ ያየናቸው አራት መስፈርቶች ናቸው። ክርክር የሚነሳው አንድ አካል ሀገር የሚሆነው የሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽንን አራቱን መስፈርቶች ሲያሟላ ነው ወይስ በሌሎች ሀገራት እውቅና ሲሰጠው? በሚለው ላይ ነው። በዚህ ረገድ ሁለት መሰረታዊ ንድፈ ሐሳባዊ ክርክሮች እንዳሉ በዘርፉ የተጻፉ ድርሳናት ያሳያሉ። የመጀመሪያው አንድ አካል ሀገር የሚሆነው የሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽንን አራቱን መስፈርቶች በተግባር ሲያሟላ ነው እንጂ በሌሎች ሀገራት እውቅና ሲሰጠው አይደለም በማለት ይከራከራል። የሌሎች ሀገራት እውቅና የሚጠቅመው የአንድ አካልን ሀገርነት (Statehood) ለመፍጠር ሳይሆን የተፈጠረውን እውነታ ለማመንና ለመቀበል ወይም "አንተ ሀገር መሆንህን እናውቃለን" ለማለት ነው። ይህ ተፈጥሯዊ/ገላጭ ንድፈ ሐሳብ (Declaratory Theory) ይባላል። ሁለተኛው አዋቃሪ ንድፈ ሐሳብ (Constitutive Theory) ሲሆን አንድ አካል ሀገር የሚሆነው የሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽንን አራቱን መስፈርቶች ሲያሟላ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራት እውቅና ሲሰጠው ነው በማለት ይሞግታል። በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሰረት እውቅና (Recognition) ለሀገርነት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው። አንድ አካል የሞንቴቪዲዮ መስፈርቶችን ቢያሟላም፣ በዓለም አቀፍ ሕግ ሀገር የሚሆነው በሌሎች ነባር ሀገራት እውቅና ሲሰጠው ብቻ እንደሆነ ይከራከራል። እውቅና ሀገርነትን ይፈጥራል፤ እውቅና ሳይሰጥ ሀገርነት የለም ማለት ነው። እንግዲህ ከላይ እንዳየነው፣ አንድ አካል ሀገር የሚሆነው የሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽንን አራቱን መስፈርቶች ሲያሟላ ነው ወይስ በሌሎች ሀገራት እውቅና ሲሰጠው? የሚለው አስቸጋሪ የሆነ አከራካሪ የሆነ ጥያቄ ነው። ሁለቱ ንድፈ ሐሳቦች—ገላጭ (Declaratory) እና አዋቃሪ (Constitutive)—እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ምላሽ ያላቸውና ጠንካራና ደካማ ጎን ያሏቸው ናቸው። ገላጭ ንድፈ ሐሳብ (Declaratory Theory) አንድ አካል የሞንቴቪዲዮ መስፈርቶችን (ሕዝብ፣ ክልል፣ መንግሥት፣ የውጭ ግንኙነት ችሎታ) ካሟላ፣ ሌሎች ሀገራት በፖለቲካዊ ምክንያት እውቅና ቢነፍጉትም እንኳ በሕግ ሀገርነቱን ስለማያስቀር የሀገርነትን ጉዳይ ከሌሎች ሀገራት ፖለቲካዊ ፍላጎትና ጫና ነፃ ቢያደርግም እውቅና የሌለው አካል፣ ምንም እንኳን ሕጋዊ ሀገር ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ መድረክ እውቅና ተነፍጎት (በተ.መ.ድ አባልነት፣ ስምምነት መዋዋል፣ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት) ሙሉ በሙሉ የመሳተፍ ዕድሉ ውስን ሆኖ ባለበት ሀገር መሆኑ ምኑ ላይ ነው? እውቅና ሳይኖር ሀገርነት ምኑ ላይ ነው? የሞንቴቪዲዮ መስፈርቶችን "አሟልቷል" የሚለውን የሚወስነውስ ማን ነው? የሚለው ገላጭ ንድፈ ሐሳብ ላይ የሚነሱ ትችቶች ናቸው። በአንጻሩ አዋቃሪ ንድፈ ሐሳብ (Constitutive Theory) በዓለም አቀፍ መድረክ ትክክለኛ ተሳትፎ ለመጀመር፣ አንድ አካል በሌሎች ሀገራት መቀበሉ ወሳኝ መሆኑን ማሳየቱ ትክክለኛ ነገር ቢሆንም አንዳንድ ሀገራት እውቅና ሲሰጡ ሌሎች ደግሞ ቢነፍጉስ? ያ አካል ለእውቅና ሰጪዎቹ ሀገራት ብቻ ሀገር ነው ማለት ነው? ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ሕግ የትም ቦታ የማይሠራበትን ግራ የሚያጋባና አስቸጋሪ ሁኔታ አይፈጥርም ወይ? እውቅና የመስጠት ሥልጣን ለነባር ሀገራት የተተወ ከሆነ ነባርና በተለይም ኃያል ለሆኑ ሀገራት የፖለቲካ ጫና መፍጠሪያ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በር አይከፍትም ወይ? የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በፖለቲካዊ ምክንያት ሊያደናቅፍ አይችልም ወይ? የሚለው በአዋቃሪ ንድፈ ሐሳብ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች (ትችቶች) ናቸው።

Previous Post Next Post

(0) comments to this article

No Reviews

Leave a reply