በድኃ ደንብ በነፃ ስለሚቀርብ ክስ (Pauper's Suits)
አንድ በፍርድ ሊወሰን የሚችል የፍ/ብሔር ጉዳይ በፍ/ቤት መታየት የሚጀምረው የክስ ማመልከቻ ለፍ/ቤት በማቅረብ ሲሆን በዚሁ መልኩ የሚቀርብ ክስ ሕግ በሌላ ሁኔታ ካልደነገገ በስተቀር ተገቢው የዳኝነት ክፍያ (Court fee) ተከፍሎበት ሊቀርብ እንደሚገባ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 213፣ 214፣ 215 እና የተለያዩ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል። ይህ ክፍያ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን (የዳኝነት አገልገሎት ለመስጠት) መንግስት ለሚያወጣቸው የተለያዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች ለመሸፈን ታቅዶ ተገልጋዩ ላይ የሚጣል የክፍያ አይነት እንደሆነ ይታወቃል። ክፍያው እንደየጉዳዩ አይነት፣ የዳኝነት ስልጣን እና የተጠየቁ አገልግሎቶች መጠኑ ይለያያል። ሆኖም የክፍያው መጠን ሰዎች ፍትሕን የመግዛት ያህል እንዳያስቆጥር እና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እንዳይፈትን የተጋነነ መሆን የሌለበት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። ምክንያቱም የክፍያው መጠን በተጋነነ ቁጥር የሰዎች ፍትሕ የማግኘት መብት አደጋ ላይ ይወድቃል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፣ የዳኝነት ክፍያ የሰዎች ፍትሕ የማግኘት መብት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ሀገራት በድኃ ደንብ ክስ በነፃ የሚቀርብበትን ሁኔታ (Pauper's suits) በሕጎቻቸው ሥርዓት የሚያበጁለት ሲሆን እኛም አሁን በስራ ላይ ባለው የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ክስ በድኃ ደንብ በነጻ ሊቀርብ ስለሚችልበት ሁኔታ ሥርዓት ተዘርግቷል። /ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 467-479 ይመለከተዋል/ በዚህም መሰረት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 467 (1) ገንዘብ የሌለውና ለማግኘት የማይችል ማናቸውም ደኃ ሰው የዳኝነት ገንዘብ ሳይከፍል ነፃ ፋይል ከፍቶ ክስ ለማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል። የሚቀርበው ማመልከቻ ከሕጉ ጋር በተያያዘው ፎርም ተዘጋጅቶ በመሐላ ቃል ተደግፎ በአመልካቹ ወይም በወኪሉ ሊቀርብ እንደሚገባ የዚሁ ሕግ አንቀፅ 468 እና 469 ያሳያል። አመልካች ገንዘብ የሌለውና በሙሉ ወይም በከፊል ለክሱ የሚያስፈልገውን የዳኝነት ገንዘብ ለመክፈል የማይችል ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይገባዋል። በድኃ ደንብ በነጻ ፋይል ለማስከፈት አቤቱታ ሲቀርብ ፍ/ቤቱ ሌላኛው ወገን መልስ እንዲሰጥበት አድርጎ የግራ ቀኛቸውን ማስረጃ በማጣራት እንዲሁም አግባብነት ባለው ማስረጃ አጣርቶ አቤቱታ አቅራቢው የገንዘብ አቅም የሌለው ድኃ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡
በሕጉ አንቀጽ 467 (1) ላይ "... ገንዘብ የሌለውና ለማግኘት የማይችል..." ተብሎ የተገለጸው ሕጉ ለማሳካት የፈለገውን የሰዎች ፍትሕ የማግኘት መብት በሚያስጠብቅ መልኩ በጠባቡ (Strict interpretation of law) ሊተረጎም ይገባል፡፡ ይህን በተመለከተ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 188406 ሕጉ በጠባቡ መተርጎም እንዳለበት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ንብረትና ገንዘብ ኖሯቸው ይህ ንብረትና ገንዘብ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በመታገዱ አሁን ላይ ለዳኝነት ገንዘቡን ለመጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ሊገኙ ይችላሉ። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሕጉን ለጥጦ በመተርጎም አቤቱታ አቅራቢ የነበረውን ገንዘብ የተጠቀመበት ስለመሆኑ አልተረጋገጠም በሚል በነፃ ዳኝነት ሊከፍት አይገባም ማለት ተገቢነት የለውም። /የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በቅፅ 20፣ በሰ/መ/ቁ. 117754 ላይ የሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ይመለከተዋል/ በድኃ ደንብ ክስ ከማቅረብ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ በድኃ ደንብ ክስ ለማቅረብ የተደነገጉት የሥነ-ሥርዓት ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑት ለተፈጥሮ ሰው (Physical person) ነው ወይስ በሕግ ሰውነት ያላቸውንም አካላት (Legal person) ጭምር ይመለከታል? የሚለው ሲሆን ይህን በተመለከተ የሰበር ሰሚ ችሎቱ በቅፅ 14፣ በሰ/መ/ቁ. 79555 ላይ የድኃ ደንብ ሥርዓቱ የተፈጥሮ ሰውንም ሆነ በሕግ ሰውነት ያላቸውን አካላት እንደሚመለከት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል። በመሆኑም አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አቅም አጥቶ በድኃ ደንብ ክስ ቢያቀርብ፣ በንግድ ሕጉ መሰረት ስለገንዘቡ አቋም (ደረጃ) ለማረጋገጥ በሚቀርብ አግባብነት ያለው የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ያለበትን የገንዘብ አቋም በማረጋገጥ በነፃ ዳኝነት ሊከፍት እንደሚችል ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል። የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 470 በድኃ ደንብ ክስ ለማስከፈት የቀረበ ማመልከቻ ተቀባይነት የሚያጣበትን ሁኔታ ይደነግጋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢው የገንዘብ ችግር ከሌለበት፣ በነጻ ለመክሰስ ያቀረበው ነገር የማያስከስስ የሆነ እንደሆነ፣ በማጭበርበር ወይም በሌላ ከፍ/ቤት ክፍያ ለመሸሽ ንብረቱን ካስተላለፈ በድኃ ደንብ ክስ ለመመስረት ያቀረበው ማመልከቻ ውድቅ ሊደረግ ይችላል፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ አንቀጽ 475 በድኃ ደንብ ክስ እንዲያቀርብ የተፈቀደለት ሰው በነጻ የመከራከር መብቱን የሚያጣበት ሁኔታዎችን (Dispaupering) ይመለከታል፡፡ እነዚህም በቀነ ቀጠሮ ቀን ችሎት ላይ አለመገኘት፣ የማወክ የማስቸገርና የተንኮለኛነት ጠባይ ማሳየት ወይም ሀብት ያለው መሆኑ መታወቁን ያካትታሉ፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ ግለሰቡ ተገቢውን የዳኝነት ክፍያ እንዲከፈል ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በመጨረሻም በነጻ እንዲከራከር የተፈቀደለት ሰው በክርክሩ ረቺ ሆኖ በተገኘ ጊዜ የተፈረደለትን ንብረት ከመረከቡ በፊት ያልተከፈለ የዳኝነት ክፍያ ከንብረቱ ላይ መቀነስ እንዳለበት የሕጉ አንቀጽ 476 ይደነግጋል፡፡ የዚህ ድንጋጌ የእንግሊዝኛው ቅጂ “… shall be recoverable from the unsuccessful party” በማለት ይገልጸዋል፡፡ የእንግሊዝኛው ቅጂ በድኃ ደንብ እንዲከራከር የተፈቀደለት ሰው በክርክሩ ረቺ ከሆነ የዳኝነቱ ክፍያ ከተረቺው አካል ላይ ሊመለስ እንደሚችል ሲገልጽ፣ የአማርኛው ቅጂ ግን የዳኝነት ክፍያው በፍርድ አፈጻጸም ከሚረከበው ንብረት ላይ ተቀናሽ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ ከዚህም በሁለቱ የሕጉ ድንጋጌዎች ቅጂዎች መካከል የትርጉም ልዩነት ያለ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የአማርኛው ቅጂ ገዥነት ይኖረዋል፡፡

(0) comments to this article
No Reviews